የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሆላንድ

የኢ.ኦ.ተ. የደብረ መዊዕ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ቤተ ክርስቲያን በኔዘርላንድ አመሠራረትና እድገት ፤

በዚህ አምድ የኢ.ኦ.ተ. ቤ/ክርስቲያን በኔዘርላንድ የደ.መ. ቅ/ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን አጀማመርና አሁን የደረሰበትንም እድገት በተመለከተ እንቃኛለን።

አጠቃላይ የቤተክርስቲያኗን እንቅስቃሴን በተመለከተ፦

ክፍል አንድ (1990 – 2005)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኔዘርላንድ በእግዚአብሔር ቸርነት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ቀስ በቀስ እድገት እያሳየ እየመጣ ነው። በወቅቱ በነበሩ ምእመናንና ዲያቆናት የተጀመረው የቤተክርስቲያናችን እንቅስቃሴ እድገት አሳይቶ እ.አ.አ. በ1994 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የቤ/ ክ አሰባሳቢ መንፈሳዊ ኮሚቴ በምዕመናኑ ምርጫ ያቋቋመ ሲሆን፡ ቀጥሎም ከሶስቱ የሰንበት ት/ቤቶች በተውጣጡ የመንፈሳዊ ኮሚቴና በካህናቱ እየተመራ ቆይቶ በእግዚአብሔር ፈቃድ በአሁኑ ጊዜ የቤተክርስቲያናን ቃለ አዋዲ በሚያዘው መሠረት በመንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ለመመራት በቅቷል። በሥሩም የአምስተርዳም፤ የዴንሃግና የሮተርዳም ሰንበት ት/ ቤቶች በየሳምንቱ ወይም በየአስራ አምስት ቀኑ የወንጌል ትምህርት አገልግሎት ይሰጣሉ። በቤልጅየም ብራስልስ ያለው ሰንበት ት/ ቤትና በቫኸኒንገን፣ በዴልፍትና በኤንስከዴ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በቅርቡ ተቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የግቢ ጉባኤያትም በዚሁ ሰበካ ሥር ናቸው። 

የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ታቦተ ሕግ ባለበት በዴንሃግ ከተማም ከሰንበት ት/ ቤት ጉባኤ ሌላ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ቅዳሜ ጠዋት የኪዳን አገልግሎት ባሉት ካህናት ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ፈቃድ አቅም እንደቻለ ሁሉ በዋና ዋና የሃይማኖታችን በዓላት በዓመት ውስጥ ከ8 ያላነሱ የቅዳሴ ስርዓት አገልግሎት ይሰጣሉ። እነዚህን የቅዳሴ አገልግሎቶችና የወንጌል ትምህርቶች ለምዕመኑ በተጠቀሱት ስፍራዎች ባሉት ካህናትና ዲያቆናት እንደዚሁም ሰባኪያን ለማዳረስ እየተሞከረ ሲሆን የሚገጥሙንን ችግሮችና ፈተናዎች በትዕግስት በማለፍ በእግዚአብሔርም እርዳታ ጭምር የቤተ ክርስቲያናችን እድገት አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ተችሏል።ለዚህ እድገት አስተዋጽኦ ካበረከቱት ውስጥ የአባቶች ጳጳሳት፡ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁም በኔዘርላንድ ነዋሪ ሆኑትና የነበሩት ምዕመናት ተሳትፎ ትልቅ ስፍራ አለው።

ቀደም ብለው ወደ ሆላንድ በመጡ ምዕመናን ጥረትና ድካም የክርስትና እምነታቸውን በባዕድ ሀገር ለማካሄድ ከተጀመረ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
እ.አ.አ በ 1992 ዓ.ም የስደተኞች ቁጥር በመበራከቱና በተለይም ራስን ለመቻል በተደረገው ጥረት በወቅቱ በነበሩት ዲያቆናት ማለትም ዲ/ን ከፈለኝ ወ/ጊዮርጊስ (በኋላም ቀሲስ ) ፣ ዲ/ን ያሬድና ዲ/ን ተረፈ የመጀመሪያው የስግደት በዓል በአምስተርዳም ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ይሄው ተጠናክሮ የትንሳኤ በዓሉም ግንቦት ወር ላይ በዴንሃግ ከተማ ከጀርመን በመጡት በቀሲስ ዶ/ር መርዓዊ መሪነት እና በዲያቆናቱ በደመቀ ሁኔታ በመከበሩ የተነሳ ምዕመኑ እምነቱን በተጠናከረ መንገድ ለማካሄድ ሊያነሳሳው ችሏል።
መጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዕንቅስቃሴዎች ላይ የጥሪ ደብዳቤ ለመላኪያና የቤተ ክርስቲያን ኪራይ ክፍያ በመፈፀም አገር አቀፉ የኢትዮጵያውያን ማህበር በሆላንድ ያደረገው አስተዋፅኦ የሚዘነጋ አይደለም።

የምዕመናን በብዛት መሰባሰብና የተጨማሪ ዲያቆናት መገኘት ማለትም የዲ/ን ታደሰና ዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ በሰንበት ትምህርት ቤቶች እየተገኙ ተምህርተ ወንጌል መስጠት መጀመር ለሰንበት ትምህርት ቤቶች መጠናከርና ለምዕመናን መሰባሰብ ረድቷል። ይህም በመሆኑ እ.አ.አ. March 1994 የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን አሰባሳቢ መንፈሳዊ ኮሚቴ የተመረጠ ሲሆን በዚህም ኮሚቴ የሰብሳቢነትን ቦታ ዘግይተው በዚያው አመት መጨረሻ ላያ ለሚመጡት ለአባ አፈወርቅ ጌታነህ በመመደብ፣ ም/ሰብበሳቢ ዶ/ር ሰርጹ በቀለ፤ እንደዚሁም ዲ/ን ከፈለኝ ወ/ ጊዮርጊስ ጸሐፊ ሲሆኑ በአባልነትም 10 የሚሆኑ ዲያቆናትና ምዕመናት እንደነበሩበት ታውቋል።
በዓመቱ መጨረሻ ላይም አባ አፈወርቅ ጌታነህ ለአገልግሎት ወደ ኔዘርላንድ በመምጣታቸው የኮሚቴው ሰብሳቢ ሆነው እንዳገለገሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚሁ ወቅት አካባቢ ላይ ቀሲስ ዳዊት ተገኝም በቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ግልጋሎታቸውን መስጠት የጀመሩበት ጊዜ ነበር።

በመቀጠልም የቤተ ክርትቲያናችን ምዕመን ቁጥር መጨመርና መሰባሰብ በአንድ ከተማ ተጀምሮ የነበረው የሰንበት ት/ ቤት ስርዓተ ቤ/ክርስቲያንና የመጽሀፍ ቅዱስ ትምህርት በሶስቱም ታላልቅ ከተሞች በመጀመሩ በስደት ላይ ያለው ምእመን ቸሩ እግዚአብሄር በፈቀደው መጠን ለረጅም ጊዜ አጥቶት የነበረውን ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት እድል በማግኘቱ ቤተ ክርስቲያናችን የበለጠ ጠንክራ ለምዕመኑ ሰፊ ግልጋሎት የምትሰጥበትን መንገድ ለማመቻቸት አባ አፈወርቅ የ3 ዓመት ቆይታቸውን ፈጽመው ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው በፊት አስቀድሞ በ 1994 ተመርጦ ብዙም ሳይቆይ ስራው አቁሞ በነበረው በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሚቴ ምትክ ወደፊት የሰበካ ጉባኤ እስከሚቋቋም ድረስ ከሶስቱም ከተሞች ሰንበት ትምርት ቤቶች ተወካዮችን ያቀፈ አንድ መንፈሳዊ ጉባኤ በ1996 አጋማሽ ላይ አቋቋሙ።

ምንም እንኳን አባ አፈወርቅ ከ3 ዓመት አገልግሎት በኋላ ኔዘርልንድን ለቀው ወደ አገር ቤት ቢሄዱም ዲ/ ን ከፈለኝ የቅስና ስልጣን መቀበላቸው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት እ. አ. አ ሚይ 1998 ዓ. ም በርሳቸው መምጣቱና በተጨማሪም ብጹዕ አባታችን አቡነ ሰላማ ለሐዋሪያዊ አገልግሎት ከእንግሊዝ ወደ ኔዘርላንድ በመጡበት ወቅት አባታዊ ቡራኪና ትምህርት በመስጠት የቤተክርስቲያን ሕንጽ አስገኚ ኮሚቴን እ. አ. አ. ሴፕቴምበር 6 ቀን 1998 ዓ. ም በምዕመኑ በማስመረጥ ማቋቋማቸው ለቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎት እድገት መሠረትን ጥሏል።

በመቀጠልም አባታችን ብፁዕ አቡነ መልከ ፄዴቅ በወቅቱ የምዕራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመው ከተቀመጡበት ከለንደን ከተማ በመጋቢት ወር 1999 ዓ. ም አጋማሽ ላይ የቅዱስ ገብርኤልን ታቦተ ጽላት ወደ ሆልንድ ይዘው በመምጣት የመጋቢት ገብርኤልን በዓል በአምስተርዳም ከተማ በደመቀ ሁኔታ አንግሰው በማክበርና ቡራኬ በመስጠት ታቦተ ጽላቱን ሆላንድ ለሚገኘው ምእመን እንዳመጡ በመግለጽ ምእመኑ ተረባርቦ አስቀድሞ መጥቶ ለነበረው በ በእመቤታችን ስም ለተሰየመው ታቦትና እንደዚሁም ለአዲሱ ለቅዱስ ገብርኤል ታቦት ማረፊያ የሚሆን ህንጻ ቤ/ ክርስቲያን እንዲገዛ አሳስበዋል። የቅ/ ገብርኤልም ታቦት ከእመቤታችን ተቦት ጋር በወቅቱ ተደርቦ ከላይ በተጠቀሰው ገዳም ውስጥ ገብቷል።

ከዚያም ባሉት ካህናትና በወቅቱ በነበረው መንፈሳዊ ኮሚቴ የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እ.አ.አ. እስከ 2002 አጋማሽ ድረስ በተቻለ መጠን ሲሰጥ ቆይቷል። ይሁን እንጂ እ. አ. አ. August 2002 ላይ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ የነበሩት የሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ከፈለኝ በድንገት ኔዘርላንድን ለቀው ወደ አሜሪካን መሄድ በቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ላይ ከባድ ችግር ፈጥሮ ነበር። ቢሆንም በወቅቱ የነበረው መንፈሳዊ ኮሚቴና እንዲሁም በሀገሪቱ ይኖሩ በነበሩና ለትምህርት በመጡ ዲያቆናትና ሰባኪያን፣ ማለትም እነ ዲያቆን ኢሳያስ አለማየሁና ዲያቆን መሀሪ መኮንን እንደዚሁም በምዕመናኑ ርብርቦሽ እ.አ.አ. 10 November 2002 አባታችን ሊቀ ካህናት ቀሲስ ዶ/ ር መርዓዊ ተበጀና ቀሲስ ዳዊት ተገኝ ባሉበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው የቤተ ክርሰቲያናችን አስተዳደር መመሪያ ቃለ አዋዲ መሰረት ሊመረጥ ችሏል።

አምላካችን የልዑል እግዚአብሄር ቅዱስ ፈቃዱ ሆኖ የሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ሙሉጌታ ስዩም ወደ ኔዘርላንድ እንዲሁም የቀሲስ መዝገቡ ካሣ ወደ ቤልጅየም በዚያን ወቅት ለትምህርት መምጣት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው አስተዳደርና አሠራር መመሪያ በሆነው ቃለ አዋዲ መሰረት የቤተ ክርስቲያናችንን አግልግሎት ለመቀጠል ታላቅ እገዛን በመስጠት ላይ ይገኛል ። በዚህም መሰረት ቀሲስ ሙሉግታ ስዩም ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ጊዜያዊ አስተዳዳሪ በመሆን ከሰበካ ጉባኤው አባላት ጋር በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

የመጀመሪያው የሰበካ መንፈሳዊ ኮሚቴ የስድስት ወር ሪፖርት እ.አ.አ. 29 March 2003 ዓ. ም ላይ በሮተርዳም ከተማ የምእመናን ጉባኤ ላይ የቀረበ ሲሆን። በዚሁ ሪፖርት ላይ በቀረቡ አንዳንድ የቤተክርሰቲያኗ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይና በወደፊት የቤተክርስቲኗ እቅድ ላይ ሰበካ ጉባኤው አስተዳደር መፍትሄ ለማፈላለግ ባደረገው እንቅስቃሴ ከድር ስቲክቲንግ ( DIR Stichting) ጋር ግኑኝነት ለመፍጠር ተችሏል።
ከድር ስቲክቲንግ ጋር በተደረጉ የጋራ ስብሰባዎችና በተደረሰው ስምምነት መሰረት ይህ ድርጅት አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ በመሸፈን በቤ/ ክ አገልግሎት ላይ የሚታዩ ነባር ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም ወደፊት የሚጠበቁትን ብዙ ሥራዎች በቅደም ተከተል በማንሳት ለመወያየትና በተለይም ሕንጻ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ ዕቅድ አቅርቦ አፋጣኝ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ሁለት ቀን ተኩል የፈጀ አንድ ጉባኤ (ሴሚናር) በሱስተንበርግ ከተማ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። በዚህም ሴሚናር ላይ የሰበካ ጉባኤው ተመራጭ አባላት፤ የሰንበት ት/ ቤት ኮሚቴ ተወካዮች፤ የሕንጻ አስገኚ ኮሚቴ ተወካዮችና ከምዕመናንም በተውጣጡ በድንሩ 22 አባላት ተሳትፈዋል። በዚህ ሴሚናር ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ያሳለፈችውን የስራ ሂደት ( ጠንካራና ደካማ ጎኖች፤ በአሁኑ ጊዜ ያለችበትነና ወደፊትም ልታደርገው የሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም የመላኩ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት ማረፊያና ኦርቶዶክሳዊ አምልኮታችንን የምስፈጽምበት የራሳችን ህንጻ ቤ/ ክርስቲን ሊኖረን የሚችልበትን መንገድ እና እንደዚሁም በሆላንድ ውስጥ በቋሚነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ካህን አባት በደሞዝ ተቀጥረው ሊመጡ የሚቻልበትን መንገድ እና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው በመወያየት በከተሉት ፍሬ ሀሳቦች ላይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ስካሁን ድረስ የምንፈልገው ቤ / ክ ምን ዓይነት የሕንጻ ይዘት አንደሚኖረው፣ የሚያስፈልገን የቦታ ስፋትና አጠቃቀሙን በተመለከተ እንዲሁም የአፈላለጉ ዘዴ ጨምሮ በጥናት የተደገፈ መረጃ ባለመኖሩ፡ የዚህ ሞያና ልምድ ያለውን DE Verandering የሚባል ድርጅትን DIR Stichting የተባለወው ኢትዮጵያዊ ድርጅት አፈላልጎ ያገኘውን በሰሚናሩ ላይ ጋብዞ ባለሞያተኞቹ አስፈላጊው ማብራሪያ አቅርበዋል።
የቀረበውም ድርጅት ለቤተክርስቲያኑ ሕንጻ ሥራ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶችን በማፈላለግ ልምድ እንዳለውና ባለው ሙያና ልምድ ከቤተክርስቲያኗ አስተዳደር ጋር አብሮ ለመስራት ፈቃደኝነቱን ቢገልጽም ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ይፈጃል ተብሎ ከሚገመተው የገንዘብ መጠን ውስጥ ምዕመኑ መሸፈን የሚገባውን ድርሻ ይወጣ ዘንድ መነሻ ካፒታላችንን ከፍ ለማድረግ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ መቶ ሺህ ዩሮ ማሳየት ይቻል ዘንድ አቅሙ ለመክፈል የፈቀደ ሁሉ በነፍስ ወከፍ በዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ 500 (አምስት መቶ) ዩሮ እንዲያዋጣና አቅሙ የማይችል ደግሞ የቻለውን ያህል እንዲከፍል ስምምነት ላይ ተደርሧል።

• የ DE Verandering ድርጅት ባቀረበው የአሠራር ስልትና ከኛ ቤ/ክ ጋር አብሮ ለመስራት ባሳየው ፈቃደኝነት በመነሳት ሰፊ ውይይት ተደርጎ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ባለው ኃላፊነትና መመሪያ መሰረት ከድርጅቱ ጋር አስፈላጊውን ውል በመፈጸም ሥራውን እንዲቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሧል።
• የሕንጻ ቤ/ክ ማፈላለጉን ጥናት ለማካሄድ ከአጥኚው ድርጅት የቦታ ጥናት ቅደም ተከተሎች ከየትኛው ከተማ ይጀመር ? የሚል ጥያቄ በማቅረቡ ምላሽ ለመስጠት ብዙ የሃሳብ ልውውጥና ውይት ከተደረገ በኋላ አስታራቂ ሃሳብ ባለመገኘቱ ጸሎት ተደርጎ እጣ እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሶ በሚከተለው ቅደም ተከተል መሰረት የህንጻ ቤ / ክርስቲያኑን ለመግዛት ወይንም ለመገንባት ከተሞቹ ተስነዋል። በዚህም መሰረት ሮተርዳም፤ አምስተርዳም፤ ዲንሃግና ላይደን ሆነው ተመድበዋል። ከላይ የተጠቀሱት አራቱ ከተሞች ለእጣው በእጩነት የቀረቡበት ምክንያት፤ በ ስዎስቱ ትላልቅ ከተሞች ብዙ የቤተ ክርስቲያናችን የሚኖር በመሆኑ ሲሆን የላይደን ከተማ ደግሞ ለስዎስቱ ከተሞች አማካይ ቦታ እንደሆነ በማሰብ ነው። 

ሆኖም ሕንጻ ቤ/ክ እግዚአብሔር በፈቀደበት ቦታ፤ በጥናቱ ውጤትና የምዕመኑና የአባቶች ተሳትፎ እንዲሁም የጋራ ውሳኔን በማጣጣም የሚፈጸም መሆኑን በዕለቱ የተገኙት የሰሚናሩ ተሳታፊዎችም ያመኑበት ሲሆን የሰበካ ጉባኤው ይህንኑ በተመለከተም በተለያየ ወቅት መግለጫ ሰጥቶበታል።
• ቋሚ አባት ካህን ሊመጡልን የሚቻልበት መንገድ፤ የሚያስፈልገውንም ወጪ ሁሉ ጥናታዊ በሆነ መልኩ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደዚሁም ልዑል አምላካችን እግዚአብሄር ክብር ምስካና ይግባውና በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ምክንያት በመካከላችን ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታና ቀሲስ መዝገቡ ( በቤልጄም ) ስለሚገኙ ለጊዜው ካህን አባት እንዲመጡ የሚደረገውን ጥረት ለህንጻ ቤተ ክርስቲያን ፍለጋ ላይ እንዲውል ጉባኤው ተስማምቶ ወስኗል። ጉባኤው ለዚህ ውሳኔ እንዲበቃ አጋዥ የሆነው ሌላው ምክንያት ደግሞ፦ ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ከተገኘ እዚያው ውስጥ የካህን መኖሪያ ስለሚኖር የካህን አባት መኖሪያ ችግር በዚያው እንደሚፈታ በማመን ነው።

እ.አ.አ. 30 November 2003 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያኗ የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ 2 ኛውን ሪፖርት በዴንሀግ ከተማ አጠቃላይ የምዕመናን ስብሰባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያንዋ የእድገት አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ተቋቁሞ የነበረው የሕንፃ ኮሚቴው የስራ ዘመኑን ሪፖርት አቅርቦ ለሁለተኛ ጊዜ የሕንፃና ልማት ኮሚቴ አባላትን ለማስመረጥ ተችሏል።
የኢ.ኦ.ተ. ቤ/ክ በኔዘርላንድ ደብረ መዊዕ ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ ሥር የተቋቋሙትና የሚቋቋሙት ሰንበት ት/ ቤቶችና ሌሎች የተለያዩ የቤተክርስቲያን ኮሚቴዎች ሁሉ በዚህ በሥራ ላይ ባለወ ሰበካ ጉባኤ የበላይ አስፈጻሚነት ሥር የሚተዳደሩና እንደ አስፈላጊነቱ ካለው መተዳደሪያ ደንቦችና መመሪያዎች በተጨማሪ የየራሳቸውን የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት ሰበካው ሲያጸድቅላቸው ይመሩበታል ይተዳደሩበታልም።
የሰበካ ጉባኤው በሆላንድ ላለችው የ ኢ.ኦ.ተ. ቤ/ ክርሲቲያን አዲስ በመሆኑና አባሎችም ለሀላፊነቱ አዲስና ልምድ የጎደላቸው በመሆናቸው ብዙ ስራዎች የታሰቡትን ያህል ያልተሰሩ ቢሆንም ለእያንዳዱ አባል የሰበካ ጉባኤ መመሪያና የስራ ድርሻ በማዘጋጀት እግዚአብሄር በፈቀደው መጠን እና እንደዚሁም በአባቶች ምክርና ርዳታ አሁን ላለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ምዕመኑም ከአሁን በፊት ታይቶ የማይታወቅ ህንጻ ቤ/ ክርስቲያን እንግዛ በሚል ጠንካራ መንፈስ ገንዘብ ለማዋጣት እ. አ. አ. June 13 2004 በ Amstelveen ከተማ ለሽያጭ ቀርቦ ልንገዛው በድርድረ ላይ በነበረው የአይሁዶች የፀሎት ቤት ታላቅ ትምህርትና በጥናት ላይ የተመረኮዘ ቤተ ጸሎቱ የሚያወጣው ዋጋና ከምእመናኑ የሚጠበቀው አማካይ ወርሀዊ ክፍያ ላይ ገለጻ ከተደረገ በኋላ የቃል ኪዳን ሰነድ በመፈረም ክፍያውን በቤተ ክርስቲያናችን የህንጻና የልማት ኮሚቴ የፖስት ባንክ የሄሳብ ቁጥር ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል። ይህን መሰልም ታላቅ ጉባዔ October 10 2004 በ14 ፡00 ጀምሮ በሮተርዳም ጸሃዬ ጽድቅ የሰንበት ት/ ቤት መሰብሰቢያ ቤ/ ክርስቲያን ውስጥ ሊደረግ ተወስኗል።
ከዚሁ ጋር አያይዘን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሆላንድ በመምጣት በቅዳሴ በትምህርትና በቡራኬ ያገለገሉ አባቶችን በዝርዝር አቅርበናል።
 
• ከ 1979 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ፣ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ( ከጀርመን ) በተደጋጋሚ፣
• በመስከረም 1981 ዓ.ም. በብጹዕ አባታችን አቡነ መቃሪዎስ ፣
• በ 1985 ዓ.ም. ብጹዕ አባታችን አቡነ ዮሐንስ ፣
• ከ 1987-1990 ዓ.ም አባ አፈወርቅ ጌታነህ ፣ በቋሚነት
• ቀሲስ ብርሀኑ ( ከለንደን፤ በተደጋጋሚ ) ፣
• ቀሲስ ሰለሞን ( ከለንደን፤በተደጋጋሚ ) ፣
• ቀሲስ ደጀኔ ( ከኢትዮጵያ፤ በተደጋጋሚ ) ፣
• ቀሲሰ ሰሙ ( ከጀርመን፡ በተደጋጋሚ ) ፣
• ቀሲሰ ኮሊን ( ጃማያካዊ የኢ.ኦ.ተ. ቤ/ክርስቲያን ካህን አባት፤ ከለንደን በተደጋጋሚ ) ፣
• ከ 1985-1994 ዓ.ም ዲያቆን ከዚያም ቀሲስ ከፈለኝ ወልደ ጊዮርጊስ በቋሚነት፣
• በሀምሌ ወር 1995 ዓ.ም. ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አምስተርዳም ቅዳሴ በማድረግ ምእመናኑን የባረኩ ሲሆን በሮተርዳም ከተማም ቃለ እግዚአብሔርንና ቡራኬ ከሰጡ      በኋላ በሆላንድ ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ያላትን ስያሜ " የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን በኔዘርላንድ የደብረ መዊዕ ቅዱስ ገብርኤል " ብለው ሰይመውታል።
• ሀምሌ 1995 ዓ.ም. አባ ላዕከ ማርያም ( ከጀርመን ) ፣
• ሀምሌ 1995 ዓ.ም. ሊቀ ካህናት ብርሀኑ ገ/አማኑኤል ( ከኢትዮጵያ ) ፣
• ከ ነሀሴ 1995 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አባ ኃ/ገብርኤል ግርማ (ከኢንግላንድ ) በተደጋጋሚ ።

በመጨረሻም የሰበካ መንፈሳዊ አመራር ኮሚቴ በሆላንድ ያለው ምዕመን ስለ ሀይማኖቱና ስለ እምነቱ እንደዚሁም ስለ እናት ቤ/ ክርቲያኑ የበለጠ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ከሁሉም በላይ ልዑል እግዚአብሄር በአምሳሉ የፈጠረውን ሰውነቱን ቤተ መቅደስ ያደርግ ዘንድ ትምህርትና እውቀት ሊያገኝ የሚችልበት ታላቅ ዐውደ ርዕይ (ኤግዚብሽን) ጥቅምት 13 እና 14 1997 ዓ.ም (እ.አ.አ. 23 እና 24 October 2004) በዴንሃግ ከተማ አቅርቧል። ስለ ዐውደ ርዕዩ ይዘት፣ ለመረዳት እዚህ ላይ ይጫኑት።
በመጨረሻም በቋሚነት ተመድበው በሙሉ ጊዜ የሚያገለገለግሉና የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር የሚመሩ አባት እንዲመደቡ በሚለው ሀሳብ ላይ የሰበካ ጉባዔው በስፋፋት ከተወያየ በኋላ አሁን በት ምትምሕርት ላይ ያሉት ካሕናት አባቶች የሚያገለግሉት በትርፍ ጊዜያቸው ስለሆነና ትምሕርታቸውን ጨርሰው ሲሄዱ የግድ ቋሚካህን ስለሚያስፈልግ ከአሁኑ ይህን ኃላፊነት ተረክበው ሊመሩ የሚችሉ እና በሥራ ልምድም ሆነ በቤተ ክርስቲያን በቂ ችሎታ ያላቸው አባት ከወዲሁ መፈለግ አለብን በሚለው ሀሳብ ሁሉም አባላት በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል ።
በዚህ መሠረት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊና የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድ1ኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑተ መልአከ ሰላም አባ ተስፋ ማርያም ላቀ እንዲመጡ ይሁን በሚለው ሀሳብ ከተስማሙ በኋላ የሰበካ ጉባዔ አባላት በሙሉ የተፈ ራረሙበት የመጠየቂያ ደብዳቤ ተጽፎ የቤተ ክሕነቱም መልካም ፈቃድ ሆኖ ከጥር 1997 (2005) ጀምሮ የኔዘርላድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ ሆነዌ በመመደባቸው የቪዛ ፕሮሰሱ ተጠናቆ እሳቸውም የኔዘርላንድ ይመኖሪይ ፈቃዳቸውን አግኝተው በማገልገል ለይ ይገኛሉ ።

ከምንም ተነስተን ለዚህ ደረጃ እንደርስ ያበቃንን ቸር አምላካችንን እያመሰገንን ከዚህ ቀጥለን እ.አ.አ . 10 November 2002 በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የሰበካ ጉባኤ አመራር ኮሚቴ ምርጫ ላይ የተመረጡት አባላትና በጎደሉት አባላት የተተኩትን ስም ዝርዝር እናቀርባለን ።
1. ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታ ስዩም………...ጊዜያዊ አስተዳዳሪና ዋና ሰብሳቢ
2. አቶ ታደሰ ጃራ ………………………………ም/ሰብሳቢ 
3. አቶ እንግዳሸት ዳምጠው…………………...ጸሀፊ
4. ዲያቆን ዳንኤል ይፍሩ............................የስብከተ ወንጌል ክፍል 
5. አቶ ፋንታ ማንደፍሮ..............................የሰንበት ት/ቤቶች ክፍል 
6. አቶ ክፍለማርያም ሁንዴ……………………የቁጥጥር ክፍል .
7. ወ/ሮ ደብረወርቅ በቀለ ……………………ገንዘብ ያዥ 
8. አቶ ሙሉግታ ዓለም…………………………ንብረት ክፍል 
9. ወ/ሮ ሀይማኖት ሰለሞን……………………ሂሳብ ሹም
ልዑል እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ይባርክልን፤ አሜን !

ክፍል ሁለት (2006 - 2012)

ቀደም ሲል የተመረጠው የሰበካ ጉባዔ ፤ ጉባዔ ስብሰባ በቃለ ዓዋዲ ደንብ መሠረት ፤ የሶስት ዓመት የአገልግሎት ዘመኑን ስለአጠናቀቀ ፤ ቀጣይ ምርጫ እንዲደረግ ሰበካ ጉባዔው ከተስማማ በኋላ ፤ የምርጫው ቀንም የካቲት 5 1998 (Feb. 12 2006) እንዲሆንና ምርጫውን ለማስፈጸም የሚረዱ ሁኔታዎች ከማመቻቸቱ ጎን ለጎን፤ በየሰንበት ት/በቶቹ ለአገልግሎት የሚያዘጋጅ ትምህርት እንዲሰጥ ተወሰነ ። በዚህ መሠረት በሶስቱም የሰንበት ት/ ቤቶች (በአምስተርዳም በዴንሃግና በሮተርዳም) አስመራጭ ኮሚቴዎች እንዲመረጡ ከተደረገ በኋላ ። አስመራጮችም ከየተወከሉባቸው ሶስቱም
ሰ/ት/ ቤቶች 15 እጩዎችን መልምለው እንዳጠናቀቁ፤ የካቲት 5 1998 (Feb. 12 2006) በሮተርዳም ፀሀየ ጽድቅ ሰንበት ት/ቤት፤ በሆላንድ አገር የሚገኙ አጠቃላይ ምእመናን በተገኙበት ከሶስቱም ሰንበት ት/ቤቶች የቀረቡት እጩዎች ቀርበው ፤ የምርጫው ሥነ ስርዓት ተካሄዷል ።
የምርጫው ስነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ላለፉት ሶስት ዓመታት በሰበካ ጉባዔ አባልነት በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ተመድበው ላገለገሉ የሰበካ ጉባዔ አባላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል :: 

በተጓደሉት አባላት ምትክና በሚያስፈልጉ የአገልግሎት ክፍሎች ከተጠባብቂዎችና ከካህናት የተተኩ አዳዲዲስ አባላትን ያካተተው ፤ የሰበካ ጉባዔ የሥራ ድልድል የሚከተለው ነው ። 

1. አቶ ታዬ ሁሴን................ ም/ሰብሳቢና የሮተርዳም ሰ/ት/ቤት ተወካይ 
2. አቶ ዳዊት ናቅአርጋቸው......... ...ዋና ጸሐፊ
3. ቀሲስ ዳንኤል ይፍሩ.............. ..ት/ት ክፍል
4. ዲ/ን ዮሴፍ ዓለማየሁ.............. .ት/ት ክፍል 

5. ዲ/ን ኃይለ ገብርኤል............... የአምስተርዳም ሰ/ት/ቤት ተወካይ 
6. ወ/ሮ ገነት ሰብስቤ.................. ሂሳብ ክፍል
7. ወ/ሮ ማሾ ፋንታ.................... የህንፃ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ
8. ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ............. .ገንዘብ ያዥ 

9. አቶ ታደሰ ጃራ................... ...ቁጥጥር ክፍል
10. ወ/ሮ አሥራት ተክሌ............ የዴንሃግ ሰ/ት/ቤት ተወካይ 
11. አቶ ዘሪሁን ሸንቁጤ............. ንብረት ክፍል
12. አቶ አማረ ለይኩን .............. አባል ፤ ናቸው ። 

መልአከ ሰላም አባ ተስፋ ማርያም ላቀም ፤ አገልግሎቱንም ሆነ አስተዳደሩን በቋሚነት (በሙሉ ጊዜ) ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ፡ ከአዲሱ የሰበካ ጉባዔ ፤ ከሰንበት ትምሕርት ቤት ፤ እና ከህንጻ ኮሚቴ አባላት ጋር በመካከር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ። 

ከተከናወኑት ተግባራትም ጠቂቶቹ ፤ ቀደም ሲል በነበሩት አምስተርዳም ፤ ሮተርዳምና ዴንሃግ፡ ሰ/ት/ቤቶች ተጨማሪ የወንጌል ትምሕርትና የቅዳሴ መርሃ ግብሮችን አስፋፍቶ አገልግሎቱን ከመቀ ጠል ጋር በኡትሬኽትና ኢንዶቨን ሁለት ጉባዔያትን በማቋቋም ፤ ሰንበት ቤቶችን ወደ አምስት ከፍ እንዲሉ ተደርጓል ። 

ተተኪ አገልጋዮችን ከዚሁ ለማፍራት ይቻል ዘንድ ፤ በዴንሃግ ፤ ሁለት ጊዜ ፤ በዴልፍት ግቢ ጉባዔ ሁለት ጊዜ ኮርሰኞች ፤ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምሕርትና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ተምረው ተመርቀዋል ።
በተጨማሪም ፡ በግንባር ከሚያገለግሉና ለክሕነት የሚያበቃ ሥነ ምግባር ያላቸው ሶስት የሰንበት ትምሕርት ቤት ወጣቶችን በማሰልጠን ማዕርገ ዲቁና የተቀበሉ ሲሆን ፤ በዲቁና በማገልገል ላይ የሚገኝ የዲ/ን ዳንኤል የቅስና ማዕርግ መቀበልም ፤ የነበረብን የካሕናት እጥረት በመጠኑም ለማሟላት አስችሎናል ። 

መንፈሳዊ አገልግሎቱን ከማካሄድ ጎን ለጎንም ፤ የህንጻ ኮሚቴውን በማጠናከር ፤ ምእመናን ፡ ለቤተ ክርስቲያን መግዣ የሚሆን ገንዘብ የሚያደርጎት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ ቀደም ሲል በተያዘ ው ዕቅድ መሠረት ፤ የራሳችን የሆነ ቤተ ክርስቲያን ይኖረን ዘንድ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለያ ዩ ከተሞች የሚሸጥ ቤተ ክርስቲያን በማፈላለጉን ተግባር ላይ በሰፊው ተንቀሳቅሷል ።በዚሀም መሠረ ት ፡ በደቡብ ሆላንድ ሮተርዳም አካባቢ ፔርኒስ በሚባል ቦታ በተመጣጣኝና ከአቅማችን ጋር ሲተያ ይ ልንገዛው በምንችለው ዋጋ የሚሸጥ ቤተ ክርስቲያን በመገኘቱ ፡ ሁሉም የኮሚቴ አባላት ማለትም የሰበካ ጉባዔ ፡ የህንጻ ኮሚቴና የሶስቱም የስ/ት/ቤቶች የኮሚቴ አባላት በጋራ ተወያይተው የደረሱበት ን የጋራ ስምምነት ፡ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አቅርበው ፤ እንዲገዛ ካስወሰኑ በኋላ ፡ የሀገሩ ህግ በሚፈቅደ ው መሰረት ፡ ከባለሙያዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ፤ የግዢው ሂደት ሊጠናቀቅ ቸሏል ። ጸሎታችንን ሰምቶ የረጅም ጊዜ ምኞታችን በ መፈጸም የህንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት እንድንሆን ላበቃን ለኃያሉ አምላካችን ከፍ ያለ ምስጋናችን ን እናቀርባለን ።
የቤተ ክርስቲያኑ አጠቃላይ ዋጋ 315 000 ዩሮ ሲሆን ፡ ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲናችን የህንጻና የል ማት ኮሚቴ ስም በተከፈተው የባንክ አካውንት ተጠራቅሞ ከነበረው 161.000 ዩሮ ላይ የቅድሚያ ክፍ ያ 120 000 ዩሮ ከፍለን ቀሪውን 195 000 ዕዳ ከ 4.25 ጋር በ 11 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከፍለን እን ድናጠናቅቅ ከተስማማን በኋላ ፡ ከቅድሚያ ክፍያ 120 000 በተጨማሪ ለተለያዩ የሽያጭ ፕሮሰስ ማ ስፈጸሚያዎች ማለትም ለኖታሪስ ፤ ለBTW(ታክስ) ፤ እናም ሌላውን ጨምሮ በድምሩ 140,782.21 ዩ ሮ በመክፈል ተፈራርመን የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍ ተረክበናል ። 

ቤተ ክርስቲያኑ በእጃችን እንደገባም ፡ ከሰበካ ጉባዔ ፡ ከህንጻ ኮሚቴና ከሰ/ት/ቤቶች ፡ አባላት የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ። የእድሳትና ውስጡንም ሆነ ውጪውን በራሳችን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የማስተካከል ሥራው ተጠናቆ ፤ ለቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ ሐምሌ 15 1999 ( 22 2007) በብፁዕ አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ተባረኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል ። 

ምስጋና
ሥራው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ በምክራችሁ ፡ በሙያችሁ ፡ በጉልበታችሁ ፡ በገንዘባችሁና በምት ችሉት ሁሉ ቅን አገለግሎት ላበረከታችሁ ካሕናትና ምእመናን በሙሉ በእግዚአብሔር ስም ከልባችን እናመሰግናለን ። 

ማሳሰቢያ
በኔዘርላንድ አገርም ይሁን በመላው ዓለም የምትኖሩ ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተ ከታይ የሆናችሁ ክርስቲያን ወገኖቻችን ፡ ይህ የእግዚአብሔር ቤት የሁላችንም ነውና ፡ ቀሪ ዕዳችንን በቶሎ ከፍለን እናጠናቅቅ ዘንድ በጸሎታችሁ ፡ በዕውቀታችሁ ፡ በገንዘባችሁ ፡ እና በምትችሉት ሁሉ ትብብራችሁን ትለግሱን ዘንድ በታላቁ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ። 

እግዚአብሔር አምላክ አገልግሎታችንን ይባርክ 

የኔዘርላንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት


ክፍል ሶስት (2013 – 20xx)
 ይቀጥላል 



Share by: