በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

                        ትምሕርተ ሃይማኖት

1 ሀልዎተ እግዚአብሔር

ሀልዎት ፤ ሀለወ ኖረ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን ፤  የእግዚአብሔርን መኖር የምንረዳበት ትምሕርት  ነው ።
በዚህ ትምሕርት ፤ .  ስለ እግዚአብሔር ስሞች ።
.  ስለ እግዚአብሔር ባህርይ ።
. እግዚአብሔርን ስለ ማየትና አለማየት ፤ የሚሉትን እናያለን ። 

የእግዚአብሔር ስሞች እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች የገለጠው በስሙ ነው ። ዘፍ 12 ፥ 1 ። ዘፀ 3 ፥ 14 ። እኛ ሰዎችም እግዚአብሔርን የምናውቀው በስሙ ነው ። በስሙ እናምናለን ፤ ለስሙ እንሰግዳለን ፤ ስሙ ን ጠርተን እንድናለን ። በስሙ ለከበሩና ፡ ስሙ ለተጠራባቸው ፡(ቅዱሳን መላእክት ። ዘፍ 19 ፥ 1 ። ኢያ 5 ፥ 13 ። ቅዱሳን ሰዎች ፤ 1 ነገ 18 ፥ 7 ። ሮሜ 8 ፥ 30 ። የቤተ መቅደስ ንዋያት ። ዳን 5 ፥ 1 ። ቅዱሳት መካናት ። 2 ነገ 5 ፥ 17 ።) ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ።

በምድራዊ አስተዳደር በአገር መሪነት ደረጃ ያሉ ሰዎች ፤ ስማቸው ፣ ቢሯቸው∙፣ ያላቸው ነገር ሁሉ የተከበረ ነው ። ጊዜያ ዊዉና የሚያልፈው በሌሎች ሰዎች የሚተካው ሥልጣን ይህን ያህል ከተከበረ ፡በዘመን የማይለካ ፣ በሌላ የማይተካ አምላክ ፤ ያከበራቸው ፣ የማያልፍና ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳኑን የሰጣቸው ፣ በስሙ የተጠሩ ቅዱሳንማ በብዙ ሊከበሩ ይገባቸዋል ። እኛ ቅዱሳንን ስናከብር የባህርይ አማልክት ናቸው ብለን ሳይሆን እግዚአብሔር በስሙ ስላከበራቸው እነሱን ማክበር አምላካቸውን ማክበር መሆኑን ስለምናውቅ ነው ። እኛ ሰዎች እንኳን የምንወደውን ሌላው እንዲወድልን እንፈጋለን ፡የማይሳሳተውና ፍጹም የሆነው አምላክ የወደዳቸውንና ያከበራቸውን ብናከብር ያከብረናል ።   

የፍጡራን ስም የሚያገለግለው ለመለያነት ብቻ ነው ። ለምሳሌ ፀሀይ የሚባል ሰው ስሙ ለመጠሪያነት ከሚያገለግለው በቀር ፀሀይን ሊወክል አይችልም ። ሌላውም ስም ሁሉ እንዲሁ ተመሳሳይና ፡ አንዱን ከሌላው ለመለየት የሚያገለግል ነው ።
እግዚአብሔር ግን እንደ ስሙ ይሠራል ፡ነገር ግን ሁሉንም ባህርዩን የሚገልጽ አንድ ብቻ ስም የለውም ። ሁሉም ስሞቹ በየራሳቸው አንድን ሁኔታ ይገልጻሉ ።

ለምሳሌ ፤ እግዚአብሔር ። 
1.  ሀ.  እግዚእ - ጌታ     ብሔር - ዓለም = የዓለም ጌታ ። ጌትነቱን ይገልጻል ።      
 ለ.  እግዚእ - ጌታ     ወልድ
አብ - አባት       አብ
ሔር - ቸር        መንፈስ ቅዱስ
እግዚአብሔር የሚለው ቃል በአንድ ቃል ፡ሲገለጥ የዓለም፡ጌታ.ገዥ ማለት ነው ።
በተጨማሪም ፡እግዚአብሔር » የሚለው ስም ፡እግዚአብሔር አብ ፣ እግዚአብሔር ወልድ ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፤ በማለት(የሥላሴ) የሶስትነቱን ስም ይገልጻሉ ።

2. ኢየሱስ ፤ ማለት መድኃኒት ማለት ነው ፡ እሱ ሞቶ ሕይወቱን በመስጠት ዓለምን ያዳነ::

3. ክርስቶስ ፤ መሲህ ፣ መንግሥቱ የማያልፍ እውነተኛ ንጉሥ ማለት ነው ።  

4. አማኑኤል ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው ። ይህም፡ማለት ፡ አምላክ መለኮታዊ ባህርዩን ከሰው ባህርይ ጋር በማዋሃድ ፡ ፍጹም አምላክነቱን ፡ሳይለቅ ፡ ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ፡ ነው ።

5. መድኃኔ ዓለም ፤ የዓለም መድኃኒት ። ይህ ቃል ግዕዝ ሆኖ ኢየሱስ ከሚ ለው ጋር የትርጉም አንድነት አለው ። 

ኤል ፤ ኃያል አምላክ ማለት ነው ። በዚህ ዓለም ያለው የአንዱ ኃይል ከሌላው ኃይል ይበልጣል ፡የሁሉም ኃይል በመጠን ይለካል ። የእግዚአብሔር ግን ኃይሉ የማይመጠን ፣ የኃይለኞች ኃያል ፣ የብርቱዎች ብርቱ ፣ በተናቁት ወዳጆቹ አድሮ ኃይል በመስጠት ፡ ታላቅ ሥራን የሚሠራ ፤ ኃያል አምላክ ነው ።
ሌሎችም ክብሩንና ሁሉን አድራጊነቱን የሚገልጹ ስሞች አሉት ። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ባህርይና ከሀሊነት… ሙሉ ፡በሙሉ፡በሰው፡ቃላት መግለጽም ሆነ ማስረዳት ፡አይቻልም ምክንያቱም ፍጹም የሆነውን የአምላክ ባህርይ የሰዎች ውሱን አእምሮ ሊደርስበትና፡ሊወስነው  አይችልምና ። ነገር ፡ግን በእርሱ ፡አምነን ፡የዘለዓለም ፡ሕይወት እናገኝ ዘንድ እኛ ሰዎች በምንረዳው አቅም ራሱን ገለጠልን ። 

ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች ፤ ስማቸውን ፤ «ኤል» ከሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋር እያጣመሩ በመጠራት የአምላክ አገልጋዮችና ስጦታዎች እንዲሁም የኃይሉ መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸውበታል ።
ከነዚህም መካከል ፤ የሚከተሉትን እናያለን ። 

ስም

ሚካኤል ፤ (መኑ ከማከ) ማን እንደ አምላክ ማለት ሲሆን ። ሰያሜውም የአምላክ፡ ባለሟልነቱን ይገልዓል

ገብርኤል ፤ ገብር አገልጋይ = የእግዚአብሔር አገልጋይ ማለት ሲሆን የሁሉም መላእክት ስማቸው ኤል ከሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋር የተጣመረና ትርጉሙም ተግባራቸውን የሚገልጽ ነው ።

ከሰዎች መካከልም « ኤል » ከሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋር ተጣምሮ የሚጠራ ስም የጥቂቶችን እንደሚከተለው እናያለን ። 

ሳሙኤል ፤    ሳሙ - ስም   ኤል - አምላክ  = የእግዚአብሔር  ስም ።
ኤልያስ ፤    ኤል - አምላክ   ያስ - አምላክ = እግዚአብሔር አምላክ ነው ።
ዳንኤል ፤    ዳን - ዳኛ   ኤል - አምላክ = እግዚአብሔር ዳኛ ነው ።
ሕዝቅኤል ፤  ሕዝቅ - ብርታት  ኤል - አምላክ = እግዚአብሔር  ብርታት ነው ።
ኢዩኤል ፤    ኢዩ - አምላክ  ኤል - አምላክ = እግዚአብሔር አምላክ ነው ።
ናትና ኤል ፤  ናትና - ስጦታ  ኤል - አምላክ = የእግዚአብሔር ስጦታ ። 

2  የእግዚአብሔር  ባህርይ

የእግዚአብሔር መለኮታዊ ባህርይ በሰው አእምሮ የማይመረመርና የማይወሰን ረቂቅ ነው ። በዓለም ያለውን ማንኛውንም ነገር መመራመርም ሆነ ለሌላውም ማስረዳት ይቻላል ።
የመለኮትን ባህርይ ግን ሙሉ በሙሉ ተመራምሮ የሚያውቅም ሆነ የሚያስረዳ ማንም የለም ። ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በገለጹልን መሠረት እንደሚከተለው ለመግለጽ እንሞክራለን ።

2.1 እግዚአብሔር መንፈስ (ረቂቅ) ነው

እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእምነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል ። ዮሐ 4  ፥ 24 ። በማለት ጌታችን እንደተናገረ እግዚአብሔርን ስናምን በዓይናችን አይተን ፣ በእጃችን ዳስሰን አረጋግጠን ሳይሆን በመለኮታዊ ባህርዩ በሥጋ ዓይን የማይታይ አምላክ መሆኑን አምነን በመቀበል ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስንልም ። በእኛ አእምሮ የማ ይታወቅ ፤ መጠን የማይሰጠው ፤ በላብራቶሪ ምርመራ የማይደረስበት ፤ ከምርምር ውጭ የሆነ አምላክ ማለታችን ነው ።
እግዚአብሔር የፈጠረው ነፋስን እንኳን ከረቂቅነቱ የተነሳ በዓይናችን ማየት እንደማንችል ሁሉ ። ዮሐ 3 ፥ 8 ። ረቂቃን ፍጥረታትን የፈጠረ አምላክ መለኮታዊ ባህርዩ ሊመረመርና ሊገመት የማይችል ረቂቅ ነው ።

2.2 እግዚአብሔር በሁሉም ሙሉ ነው

ሰው በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ መገኘት የማይችል በተወሰነ ቦታ ብቻ የሚወሰን ነው ። ኤር 23 ፥ 23 ። እግዚአብሔር ግን ፍጡር የማይወስነው ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኝ ፣ (ምሉዕ በኩለሄ የሆነ) አምላክ ነው ። እግዚአብሔር በዓለም ሙሉ ነው ሲባል በዓለም ውስጥ ብቻ ተወስኖ ይኖራል ማለት ሳይሆን ዓለምን በውስጡ ይወስናል ማለት ነው ። በኢሳ 8 ፥ 1 ። “ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት ።” የሚለው ቃል እግዚአብሔር በዚህ አካባቢ ብቻ አለ ተብሎ ቦታ የማይወሰንበት ፡ ሰማይም ምድርም ዓለማት በሙሉ ግዛቱ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነው ። 

2.3 እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው

ሰዎች በዚህ ዓለም መኖር የሚችሉት በሕይወት እስካሉ ድረስ ብቻ ነው ። ጊዜያዊ የሆነው ምድራዊ ኑሯቸው በሞት ይለወ ጣል ። ዘፍ  3 ፥ 19 ። እግዚአብሔር ግን ዓለማት ሳይፈጠሩ የነበረ ፣ አሁንም እየገዛ ያለ ፣ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚ ኖር ፣ በባህርዩ ሞት ፣ በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት ዘለዓለማዊ አምላክ ነው ።

እኛ ሰዎች የተወለድንበት ቀን መጀመሪያችን ፤ የምንሞትበት ቀን መጨረሻችን ነው ፤ አምላክ ግን ሰው በመሆኑ ዘመን ቢቆ ጠርለትም ፤ ሥጋ ፡ የመለኮትን ባህርይ በተዋሕዶ ገንዘቡ ስላደረገ “ስለተዋሃደ” ፤ ዘመናት የማይቀድሙት ቀዳማዊ ዘመናትን አሳልፎ የሚኖር ደኃራዊ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ አምላክ ነው ። ራዕ 1 ፥ ፲፰ ለነበረበት መጀመሪያ ፤ የማይኖርበት መጨረሻ የለውም ፤ ለሁም ነገር መጀመሪያውም ሆነ መጨረሻው ራሱ ነው ። ዘፍ 18 ፥ 14  ዘፀ 3 ፥ 14 ።  

2.4 እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነው

እኛ ሰዎች በሕይወት ዘመናችን ማድረግ ወይም ማግኘት የምንችለው የተወሰነ ነገር ብቻ ነው ።
ለምሳሌ ፤ በዓለም ያለውን ዕውቀት ፣ ሀብት ፣ ሥልጣን፣.. ሁሉ በአንድ ጊዜ ማግኘት አንችልም ። ብዙዎቻችንም «ያለኝ ይበ ቃኛል» ብለን በተሰጠን ከማመስገን ይልቅ ሌላውን ሆነን ለመገኘት የምናደርገው ድካም በእኛነታችን ውስጥ ጉድለት እንዳለና ሁሉንም ማድረግም ሆነ መሆን እንደማንችል ያስረዳል ። እግዚአብሔር ግን ያለማንም እርዳታ በማንኛውም ሰዐት የወደ ደውን ማድረግ የሚችል ፣ ጌትነቱ ፣ ዕውቀቱ ፣ ሀብቱ ፣ የራሱ የሆነ ፤ ከማንም ምንም የማይሻ ፤ ሁሉ ያለው ፤ የማይደክም ፣ የማይሰለች ፣ የሚሳነው ነገር የሌለ አምላክ ነው ። ዘፍ 18 ፥ 13 ። ሉቃ 1 ፥ 37 ። ኢሳ 40 ፥ 2 ።

2.5 እግዚአብሔር ጥበበኛ (አዋቂ) ነው

የሰው ልጅ ይዞት የተወለደው ልቅሶ ብቻ ነው ። ሌላውን ሁሉ ፡ በማየት፣ በመስማት ፣ በመማር ፤ ከሰዎች ያገኘው ነው ። ያውም ቢሆን ያለፈውን ታሪክ ከማውራትና አሁን የሚደረገውን ከማየት በቀር ወደ ፊት የሚሆነውን ለማወቅ የሚያስችል ዕው ቀትና ጥበብ የለውም ። ዕውቀቱም ቢሆን የአንዱ ዕውቀት ከሌላው ይበልጣል ፤ በዚህ ዓለም ፍፁም የሆነ ዕውቀት የለም የተከፈለውም ቢሆን በጊዜው ያልፋል ። 1ቆሮ 13 ፥ 8 ። እግዚአብሔር ጥበቡ የባህርዩ የሆነ ፣ ያለፈውን የማይረሳ ፣ የሚያውቅ ፣ ለሰዎች ዕውቀትንና ጥበብን የሚገልጽ አምላክ ነው ። ሰው ሊያውቅና ሊመራመር የሚችለው ውጫዊውንና ግዙፉን ነገር ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ግን ልብና ኩላሊትን (በሰው ህሊና የታሰበውን) አስቀድሞ የሚያውቅ አምላክ ነው ። መዝ 7 ፥ 9 ።

2.6 እግዚአብሔር ቅዱስ ነው

ቅድስና የእግዚአብሔር የባህርዩ ሲሆን “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ዘሌዋ 19 ፥ 2 ። 1 ዼጥ 1 ፥ 15 ። ባለው ቃል መሠረት ቅዱሳን መላእክትና በሥራቸው ለቅድስና የበቁ ሰዎችም ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ ።
የመላእክትና የሰዎች ቅድስና ግን ፡ በሥራ የሚገኝ ፣ በሃይማኖት የተፈተነ ፣ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ የፀጋ ቅድስና ነው ። የፍጡራን ቅድስና ፡ደረጃ አለው ከአንዱ የሌላው ይበልጣል ። 1 ቆሮ 15 ፥ 41 ። የእግዚአብሔር ቅድስና በመጠን አይወሰንም ፤ እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ማንም የለምና ። ኢሳ 6 ፥ 3 ። ዕንባ 1 ፥ 13 ።

2.7 እግዚአብሔር ቸር ነው

የሰው ልጅ ቸርነቱ (ልግስናው) በኪሱ ያለው ሳንቲም እስኪያልቅ ፤ እሱንም ቢሆን የሚሰጠው ተለምኖ ነው ። እግዚአብ ሔር
ሁሉ ያለው ፣ ያለ ንፍገትና ያለ መሰሰት ለጋስ ፣ ስጦታው የማያልቅበት ፣ ኃጥዕ ጻድቅ ሳይል በቸርነቱ ለሁሉ ያለ አድልዎ የሚያድል ማቴ 5 ፥ 41 ። ሳንለምነው የሚያስፈልገንን አውቆ የሚሰጠን ፣ ቸር አምላክ ነው ። ማቴ 6 32 ። ሰው የሚሰጠው ከሌላው ያገኘውን ነው ፤ ወደዚህ ዓለም የመጣው ራቁቱን ነው ፤ ወደ ምድር ሲመለስም የሚያስከትለው ነገር የለውም ። ኢዮ 1 ፥ 21 ። 1ጢሞ 6 ፥ 7 ። እኛ ለሌሌሎች የምንሰጠው ከተረፈን ብቻ ነው አምላካችን ግን ለእኛ የሰጠን ራሱን ነው ። ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም ። ዮሐ 15 ፥ 13 ። ሰው የሚሰጠው ለወዳጁ ፣ ለወገኑ ፣ ለሚመስለው… ነው እግዚአብሔር ግን ጠላቶቹ ሳለን ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ከራሱ ጋር አስታረቀን ፤ ከዘለዓለም ሞትም አዳነን ። ሮሜ  5 ፥ 10 ።

2.8 እግዚአብሔር ፍቅር ነው

ሰው ወዳጁን ይወዳል ለማይወደው ግን ቦታ አይሰጥም ፤ እንዲያውም ከተመቸው ከመበቀል ወደኋላ አይልም ። እግዚአብ ሔር ግን እየበደልነው ለንስሐ እስክንዘጋጅ በብዙ ታግሶ ይወደናል ። ሮሜ 2 ፥ 4 ። የሰው ፍቅሩ ተለዋዋጭ ፣ ወረት ያለበት ፣ ጊዜያዊ ነው ። ሰው ለጥቅም ብሎ ወዳጁን ይገድላል ። አምላካችን ፍቅሩ የማይለካ ፣ ለእኛ ለጠላቶቹ የሞተ ፤ ኢሳ 53 ፥ 1 ፥12 ። የሠራነውን ሁሉ በቸርነቱ ይቅር ብሎ ከበደል የሚያነጻን አምላክ ነው ። ኢሳ 1 ፥ 18 ። እግዚአብሔር ፈቅደን እንድንገዛለት ይፈልጋል እንጅ ፤ ማንኛችንንም አስጨንቆ አይገዛንም ። 1 ዮሐ 1 ፥ 8 ።

2.9 እግዚአብሔር በእውነት የሚፈርድ እውነተኛ ዳኛ (ፈራጅ) ነው

እግዚአብሔር ለሰዎች የዳኝነት ሥልጣን የሰጣቸው ትክክለኛ ፍርድ እንዲፈረዱ ነው ። ማንም ቢሆን እውነት መፍረድ እንዳለበት ህሊናው ይነግረዋል ። በሐሰት ስንፈርድ በመጀመሪያ የሚወቅሰን ህሊናችን ነው ። የህሊና ወቀሳን የማይፈራ ማንንም ሊፈራ አይችልም ። ዳኞች ፡ በዘመድ ፣ በጥቅማ ጥቅም ፣ በዓላማ መመሳሰል ፡ እና በሌላም ፍርድ ሊያዛቡ ይችላሉ ። እግዚአብሔር ግን ከማንም ምንም የማይፈልግ ፣ ከእውነት ጋር ደስ የሚለው ፣ ፍርዱ ትክክለኛ የሆነ አምላክ ነው ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይከፍለዋል ። ራዕ 22 ፥ 12 ። መዝ 36 ፥ 28 ።

3. እግዚአብሔርን ስለ ማየትና አለማየት

3.1 የእግዚአብሔርን መኖር የምናረጋግጠባቸው ነገሮች

በዓለማችን ያሉት ነገሮች ሁሉ የአምላክን መኖር የሚገልጹ ቢሆኑም የተወሰኑትን በማስረጃነት እናያለን ። አንድን ሰው ዘመ ናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅመን ድምፁን በመስማት ወይም በአካል በማየት መኖሩን መረዳት እንችላለን ። የእግዚአብሔርን መኖር የምናውቅባቸው መንገዶች ግን ከዚህ የተለዩና በሚከተሉት መንገዶች የሚገለጹ ናቸው ።         

3.2  ሥነ ፍጥረት

“ራሱን ያለ ምስክር አልተወም” ። የሐ ሥ 14 ፥ 17 ። በአንድ ባለሙያ (በፋብሪካ) የተሰሩ ነገሮች ሰሪያቸውን እንደሚያስተዋውቁና እንደሚያስመሰግኑ ሁሉ ፍጠረታትም በእርሱ እንደተፈጠሩና እንደሚመሩ ስለ እግዚአብሔር መኖር ምስክሮች በመሆን ፈጣሪያቸውን ያስተዋውቃሉ #
“የማይታይ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ይታወቃል” ። ሮሜ 1 ፥ 20 ። ባለሞያ በሰራቸው ስራዎች እንደሚታወቅ ሁሉ እግዚአብሔርም በፈጠራቸው ፍጥረታት ይታወቃል ። በምድራችን በራሱ የተገኘ ምንም ነገር የለም ፡ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረ እግዚአብ ሔር ነው ።መዝ 23 ፥ 1 ። ሰዎች ለሚሰሯቸው ስራዎች በዲዛይንነት የሚጠቀሙት የአምላክ ስራ የሆኑ ፍጥረታትን ነው ። የሰዎች ሥራ ፋሸኑ ያልፋል በሌላ ስልጣኔ ይተካል ። የአምላክ ስራ ግን የማይጠገብ ፡የማይሰለች ፡ ሁሌም አዲስ ነው ። ፍጥረታት እግዚአብሔር እንደፈጠራቸው በዝምታ ይናገራሉ ይመሰክራሉም  ። ኢዮብ 12 ፡7-9 ። መዝ 18 ፥1 ።    

3.3 የሰዎች ህሊና ምስክርነት

የሰዎች ህሊና ስለ እግዚአብሔር መኖር ምስክር ነው ። ክፉ ሲሰራ ይፀፀታል " መልካም በሚሰራበት ወቅት ደግሞ ደስተኛ ይሆናል  ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችም ቢሆኑ በህሊናቸው አውቀው ጥፋተኛው የሚቀጣበትን ህግ ያወጣሉ ።  ሮሜ 2 ፥ 19 ። ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ነገር “እሱ ያውቃል” በማለት ለእግዚአብሔር ይሰጣሉ ። ምንም እንኳን ክፉ ቢሰሩ ለሁሉም እንደስራው የሚከፍል አምላክ እንዳለ በህሊናቸው ያምናሉ ፡ ሰው አምላኩን ይመስላል የተባለውም በመልካም አስተሳሰቡ (ህሊናው) ነው ።

3.4 የታሪክ ምስክርነት

ታሪክ ያለፈውንና እውነት የሆነውን ነገር ለአዲሱ ትውልድ የሚያስረዳ ሲሆን ፤ በዓለም ላይ የተፈፀሙና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉ ታሪኮች ስለ እግዚአብሔር መኖር ግልጽ ምስክርነት ይሰጣሉ ።

ለምሳሌ እስራኤል በግብፅ አገር ለ430 ዓመታት መኖራቸው በታሪክ ተመዝግቧል ። ይህ ታሪካዊ ድርጊትም የተፈጸመው በእ ግዚአበሔር ጥበብ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ። ዮሴፍ በመጀመሪያ ወደ ግብፅ ወርዶ ባለስልጣን በመሆን ለወገኖቹ  ከሀገራቸው መፍለስና ለጊዜውም ቢሆን የተሻለ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ ምክንያት እንዲሆን ያደረገና ዘፍ 41 ፥ 39 ።
ሙ ሴ በአስቸጋሪ ወቅት በአስደናቂ ሁኔታ ተወልዶ በቤተ መንግስት እንዲያድግና በኋላም እስራኤልን እየመራ ከግብፅ ወደ ከነዓን እንዲያወጣ ያደረገ እግዚአብሔር ነው ። ዘፀ 3 ፥ 1 ። ሌሎችም በዓለም ታላላቅ የተባሉ ታሪኮችን በማስተዋል ከተረዳና ቸው የእግዚአብሔር ኃያልነትና ሁሉን አድራጊነት እንደተገለፀባቸው ማወቅ እንችላለን ።

በሌላም በኩል በዓለም ታሪከ ትልቅ ቦታ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር መኖርና ስለ ድንቅ ስራዎቹ  እንዲሁም በወዳጆቹ ላይ አድሮ ያደረጋቸው ተአምራትና መለኮታዊ ኃይሉን ነው ። በተጨማሪም የእግዚአብሔር ስም የተጠራባቸው “ፀበሉ ፤ እምነቱ ፤ መስቀሉ….ተአምራት ሲያደርጉ ፤ ህሙማን የእግዚአብሐርን ስም ጠርተው ፤ መዳናቸው እውነተኛና ህያው ምስክር ናቸው  ። በማስተዋል ለሚ ገነዘበው በዓለም ላይ የእግዚአብሔር ኃይል ያልተገለጠበት የታሪክ ክፍል የለም ።

3.5 እግዚአብሔርን የማናይበት ምክንያት ።

በእርግጥ እግዚአብሔር ለአብርሐም በ፫ ሰዎች አምሳል ። ዘፍ 18 ፥ 1 ለኢሳይያስ በንጉሥ አምሳል ። ኢሳ 6 ፥ 1 ። ለሌሎችም ወዳጆቹ በተለያየ መንገድ ቢገለጽላቸውም እሱ በወደደውና እነሱ ማየት በሚችሉት መጠን እንጅ እግዚአብሔርን በመለኮታዊ ባህርዩ ያየው ማንም የለም  ። ዘፀ 33 ፥ 20 ። ዮሐ 1 ፡18  ። ማቴ 17 ፥ 6 ።   

4  እግዚአብሔርን በዓይናችን የማናይባቸው ምክንያቶች

1.  ስለ  ታላቅነቱ
2.  ስለ  ብርሃናዊነቱ (አንፀባራቂነቱ)
3.  ስለ  እሳትነቱ (አቅላጭነቱ)
4.  ስለ  ረቂቅነቱ
5.  ስለ  ድምፁ አስፈሪነት…. ነው ።

4.1 የአግዚአብሔር ታላቅነት

በዚህ ዓለም ያሉ ፍጥረታት መጠናቸው ከአንዱ የሌላው ያንሳል ወይም ይበልጣል ። እያንዳንዳቸውም መለኪያ አላቸው ። ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት ስንማር ግን ይህን የዓለም ቀመር ከህሊናችን ማውጣት አለብን ። ምክንያቱም የእግዚአብሔር የሆነን ነገር ሰው በሥጋዊ ዕውቀቱ ተመራምሮ ሊደርስበት አይችልምና ። ነቢዩ “ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት” ። ኢሳ 66 ፥ 1 ። በማለት የተናገረው በሰማይና በምድር ብቻ ይወሰናል ለማለት ሳይሆን ሰማይም ምድርም በእኔ ግዛት ውስጥ ናቸው ፤ እኔ በሁሉም እገኛለሁ ፤ ፍጥረታትን እኔ እወስናቸዋለሁ እንጅ እነሱ አይወስኑኝም ለማለት ነው ። እኛ ሰዎች በአምላክነቱ ውስጥ ያለችውን ዓለም እንኳን በአንድ ጊዜ ማየት አንችልም ። እግዚአብሔርን የማ ናየው ፤ ዓለማትን የሚወስንና ከምናስበው በላይ  በእጅጉ ታላቅ በመሆኑ ነው ።

4.2 የእግዚአብሔር ብርሃናዊነት (አንፀባራቂነት)

ሰው ማየት የሚችለው የብርሃን መጠን ማየት በሚችለው ልክ ከሆነ ብቻ ነው  ። ከዚያ ከበዛም ሆነ ካነሰ ማየት አይችልም  ።
ለምሳሌ የፀሀይን ብርሃን ወይም ሌላ ከፍተኛ የብርሃን ነፀብራቅ ሙሉ በሙሉ በዓይን ማየት አይቻልም ። ዘፀ 34 ፥ 27 ። ሙሴም እንኳ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር በሲና ተራራ ቆይቶ ከተመለሰ በኃላ የፊቱ ብርሃን ስለ አንፀባረቀባቸው  እስራኤል ማየት አልቻሉም ነበር ። የሰው ልጅ ፤ ለፍጡራንን በፀጋ የተሰጠ የብርሃን ነፀብራቅን ተቋቁሞ ማየት ከልተቻለ የፈጣሪውን መለኮታዊ ብርሃን የማየት አቅም እንደየት፡ሊኖረው፡ይችላል፡? ማቴ 17 ፡ ፥ 6 ።                                               

4.3  የእግዚአብሔር እሳትነት (አቅላጭነት)

በተፈጥሯቸው ከፍተኛ የሆነ የሙቀት (አቅላጭነት) ባህርይ ባላቸው ነገሮች አካባቢ ለመኖር እንደማይቻል ይታወቃል ።
ለምሳሌ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ፤ ከፍተኛ የሙቀት አየር ያለበት አካባቢ መኖር አይቻልም እነዚህ ፍጡራን ሲሆኑ ይህን ያህል የማቃጠል ኃይል ካላቸው ፤ እነዚህን የፈጠረ አምላክማ መለኮታዊ ባህርዩ ከምናስበው በላይ አቅላጭ (እሳትነት ያለው) በመሆኑ ሰው አይቶት በፊቱ መቆም አይችልም  ። ዘፀ 33 ፥ 20 ።

4.4  የእግዚአብሔር ረቂቅነት

ነፋስ (አየር) ረቂቅ ነው ። ድምፁን እንሰማለን ከየት እንደሚመጣ ወዴትም እንደሚሄድ ግን አናውቅም ሌሎችም በዓይናችን የማናያቸው ብዙ ረቂቃን ነገሮች አሉ ከነፋስ ነፍስ ፤ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ ። እነዚህ ረቂቃን በመሆናቸው ማየት ካልቻልን ሁሉንም የፈጠረ አምላክ ፤ መለኮታዊ ባህርዩ ማሰብና መገመት ከምንችለው በላይ ረቂቅ በመሆኑ በዓይናችን ልናየው አንች ልም እግዚአብሔር መንፈስ ነው ፤ የሚሰግዱለትም አይተው ሳይሆን ፤ በመንፈስ ይሰግዱለታል ተብሏልና ። ዮሐ 4 ፥ 24 ።    

4.5  የእግዚአብሔር የድምፁ አስፈሪነት

ጆሯችን መስማት የሚችለው የድምፅ መጠን አለው ፤ ከአቅሙ በላይ ድምፅ ከሰማ የጤና መታወክ ሊደርስበት ይችላል ። አንዳንድ ጊዜ መስማት ከምንችለው በላይ የሆኑ ድምፆች ሲያጋጠሙን ጀራችንን በእጃችን በመድፈን እንከላከላለን በዓለማ ችን መስማት ከምንችላቸው በላይ የሆኑ ብዙ ድምፆች አሉ ።
እስራኤል የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት ከመፍራታቸው የተነሳ ፤ ሙሴን “እንዳንሞት እግዚአብሔር አይናገረን አንተ ተናገረን” ይሉት ነበር ። ዘፀ 20 ፥ 19 ። በሌላም በኩል አይሑድ ጌታን ሊይዙ በመጡበት ሰዓት “የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ቁመው መስማት ስላልቻሉ መሬት ላይ ወደቁ ። ዮሐ 18 ፥ 4 ። አምላክ በሥጋ በተገለጠበትም ሆነ በሌላ ጊዜ ሰዎችን የሚያነጋግራቸው መስማት በሚችሉት መጠን እንጅ መለኮታዊ ድምፁን ሰምቶ በህይወት መኖር የሚችል ማንም ፍጡር የለም ።
ከላይ የገለጽናቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ባህርይ በሰው አእምሮ የማይወሰንና በምርምር የማይደረስበት መሆኑን ለማስረዳት ያህል እንጅ አምላክነቱን በሙሉ ያስረዳሉ ማለት አይደለም :: የእግዚአብሔርን ይቅርና የሰውን ባህርይ እንኳን ማወቅ ይከብ ዳል  ይሁን እንጅ የእኛን ታናሸነትና ውሱንነት ፤ የእግዚአብሔርን ኃያልነት ለመረዳትና ለማወቅ ይረዳ ዘንድ ይህ ተጻፈ ።

 

biblical studies
ጥቅስ
እግዚአብሔር በአንድም መንገድ በሌላም ይናገራል። ኢዮ.33፥14
home
church services
biblical studies
kids
ቀጣይ ትምህርቶች
memebership
ሃይማኖት
ሀልዎተ እግዚአብሔር
ሥነ ፍጥረት (የዓለም አፈጣጠር)
አእማደ ምሥጢር
ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
links
contact us
songs
photos
preachings
download
The EOTC in The Netherlands, Debre Mewie St. Gebriel Church 2004